በመላው ዩኒቨረስ ራሱን ያስተዋወቀው አምላክ አሏህ አንድ ነው። አጋር የለውም። በማንነቱም ሆነ በባህሪው
አምሳያ የለውም።
قُلْ هُوَ اللَّهُ أَحَدٌ اللَّهُ الصَّمَدُ لَمْ يَلِدْ وَلَمْ
يُولَدْ وَلَمْ يَكُن لَّهُ كُفُوًا أَحَدٌ
“በል ‘እርሱ አሏህ አንድ ነው። አሏህ (የሁሉ) መጠጊያ ነው። አልወለደም፤ አልተወለደምም።
ለእርሱም አንድም ብጤ የለውም’።”
(አል-ኢኽላስ : 1-4)
وَإِلَٰهُكُمْ إِلَٰهٌ وَاحِدٌ لَّا إِلَٰهَ إِلَّا هُوَ
الرَّحْمَٰنُ الرَّحِيمُ
“አምላካችሁም አንድ አምላክ ብቻ ነው፤ ከርሱ በቀር ሌላ አምላክ የለም። (እርሱ) እጅግ በጣም ርኅሩህ
አዛኝ ነው።” (አል-በቀራ : 163)
በዚህ ዩኒቨርስ ውስጥ የሚገኝ ነገር ሁሉ ፈጣሪውም አስተናባሪውም አንድ መሆኑን ያመለክታል። ዩኒቨርሱን
የሚመራው አካል ከአንድ በላይ ቢሆን ኖሮ ስርዓቱ በተፋለሰ ነበር።
አሏህ እንዲህ ሲል እውነትን ተናግሯል፡- لَوْ كَانَ فِيهِمَا آلِهَةٌ إِلَّا
اللَّهُ لَفَسَدَتَا فَسُبْحَانَ اللَّهِ رَبِّ الْعَرْشِ عَمَّا
يَصِفُونَ
“በሁለቱ (በሰማያትና በምድር) ውስጥ ከአሏህ ሌላ አማልክት በነበሩ ኖሮ በተበላሹ ነበር።
የዐርሹ ጌታ አሏህም ከሚሉት ሁሉ ጠራ።”
(አል-አንቢያእ : 22)
مَا اتَّخَذَ اللَّهُ مِن وَلَدٍ وَمَا كَانَ مَعَهُ مِنْ إِلَٰهٍ
إِذًا لَّذَهَبَ كُلُّ إِلَٰهٍ بِمَا خَلَقَ وَلَعَلَا بَعْضُهُمْ
عَلَىٰ بَعْضٍ سُبْحَانَ اللَّهِ عَمَّا يَصِفُونَ
“አሏህ ምንም ልጅን አልያዘም (አልወለደም)። ከእርሱም ጋር አንድም አምላክ የለም።
ያን ጊዜ (ሌላ አምላክ በነበረ) አምላክ ሁሉ በፈጠረው ነገር በተለየ ነበር።
ከፊላቸውም በከፊሉ ለይ በላቀ ነበር። አሏህ ከሚመጥኑት ሁሉ ጠራ።”
(አል-ሙእሚኑን : 91)
አሏህ በፈጣሪነቱ አንድ ነው። የሰማያትና የምድር እንዲሁም በመካከልም ሆነ በውስጣቸው ያሉ ፍጡራን
አምላክ። ሁሉንም ነገር ፈጠረ። መጠኑን አስተካከለ። መራም። ከፍጡራኑ መካከል አንዱም በሰማይ ወይም
በምድር ውስጥ ያለችን ቅንጣት ፈጥሬያለሁ፣ አስተዳድራለሁ ወይም እመግባለሁ የሚል ክርክር አያነሳም። ይህን
ሊል አይገባውም። አይችልምም። አሏህ በአምላክነቱም አንድ ነው። ከርሱ ሌላ ለአምልኮ ተገቢ የሆነ አካል
የለም። በፍርሃትና በተስፋ የሚያድሩለት፣ የሚተናነሱለት፣ እዝነቱን የሚከጅሉት፣ የሚመኩበት፣ ትእዛዙንም
ያለ ተቃውሞ የሚፈጽምለት እርሱ ብቻ ነው። የሰው ልጆች ባጠቃላይ- ነቢያትን፣ የአሏህ እውነተኛ
ባለሟሎችን፣ ባለስልጣናትንና ንጉሳንን ጨምሮ- የአላህ ባሮች ናቸው። ራሳቸውንም ሆነ ሌሎችን መጥቀምም ሆነ
መጉዳት፣ ሕይወትን መስጠትም ሆነ መንሳት አይችሉም። ከነርሱ ውስጥ አንዱን አምላክ ያደረገ፣ በፍርሃት
የራደለት ወይም የሰገደለት ከሚገባው በላይ ከፍ አደረገው። የራሱንም ክብር አዋረደ። ስለሆነም ኢስላም
ለሰው ልጆች ባጠቃላይ፣ ለክርስቲያኖችና ለአይሁዶች በተለይ እንዲህ የሚል ጥሪ አስተላለፈ፡-
قُلْ يَا أَهْلَ الْكِتَابِ تَعَالَوْا إِلَىٰ كَلِمَةٍ سَوَاءٍ
بَيْنَنَا وَبَيْنَكُمْ أَلَّا نَعْبُدَ إِلَّا اللَّهَ وَلَا
نُشْرِكَ بِهِ شَيْئًا وَلَا يَتَّخِذَ بَعْضُنَا بَعْضًا
أَرْبَابًا مِّن دُونِ اللَّهِ فَإِن تَوَلَّوْا فَقُولُوا
اشْهَدُوا بِأَنَّا مُسْلِمُونَ
(አሊ-ዒምራን : 64)
“የመጽሐፉ ባለቤቶች ሆይ! በእኛና በእናንተ መካከል ትክክል ወደ ኾነች ቃል ኑ። (እርሷም) አላህን
እንጅ ሌላን ላንገዛ፣ በርሱም ምንንም ላናጋራ፣ ከፊላችንም ከፊሉን ከአላህ ሌላ አማልክት አድርጎ
ላይይዝ ነው፤ በላቸው። እምቢ ቢሉም፡- እኛ ሙስሊሞች መኾናችንን መስክሩ በሏቸው።”
ኢስላማዊው እምነት “የተውሂድ” “የኢኸላስ” ወይም “የተቅዋ” ቃል በመባል በሙስሊሞቹ ዘንድ በምትታወቀው
ሃረግ ይጠቃለላል። እርሷም ላኢላሀ ኢለሏህ (لا إله إلا الله) ናት- (ከአላህ ውጭ ሌላ አምላክ
የለም።) ተውሒድ በመለኮታዊ ሃይማኖቶች ሁሉ ከፍተኛ ቦታና ክብር ያለው በመሆኑ ከኑሕ እስከ ነቢያችን
ሙሐመድ (صلى الله عليه وسلم) ድረስ በአሏህ መልእክተኞች ጥሪ ውስጥ አብዩን ስፍራ ሊይዝ
በቅቷል። አሏህ ለሰው ልጆች መሪ አድርጎ የላካቸው መልእክተኞች ተግባር እርስ በርስ ተያያዥነት ባላቸው
ሁለት ጽንሰ ሃሳቦች ይጠቃለላል፡- አንደኛ፡- አሏህን (سبحنه وتعلى ) ወደ ማምለክ ጥሪ ያደርጋል።
ሁለተኛ፡- ጣኦትን ወደ መከልከል (ወደ መታቀብ) ጥሪ ያደርጋል። ቁርአን ይህን አስመልክቶ ሲናገር እንዲህ
ብሏል፡-
وَلَقَدْ بَعَثْنَا فِي كُلِّ أُمَّةٍ رَّسُولًا أَنِ اعْبُدُوا
اللَّهَ وَاجْتَنِبُوا الطَّاغُوتَ فَمِنْهُم مَّنْ هَدَى اللَّهُ
وَمِنْهُم مَّنْ حَقَّتْ عَلَيْهِ الضَّلَالَةُ فَسِيرُوا فِي
الْأَرْضِ فَانظُرُوا كَيْفَ كَانَ عَاقِبَةُ الْمُكَذِّبِينَ
(አን-ነህል : 36)
“በየሕዝቡም ሁሉ ውስጥ “አሏህን ተገዙ፤ ጣዖትንም ራቁ” በማለት መልክተኛን በእርግጥ ልከናል። ከእነሱም
ውስጥ አሏህ ያቀናው ሰው አልለ። ከእነሱም ውስጥ በእርሱ ላይ ጥመት የተረጋገጠበት ሰው አልለ። በምድርም
ላይ ኺዱ፤ የአስተባባዮችም መጨረሻ እንዴት እንደ ነበረ ተመልከቱ።”
የነብያት መቋጫ
የሆኑት ነቢዩ ሙሐመድ (صلى الله عليه وسلم) ወደ ተውሂድ ያደረጉት ጥሪ ከሌሎች ይበልጥ
የጠነከረ፣ ጥልቅ እና ዘልአለማዊ ነው። ይህ እውነታ በቁርአንና በሱንና በጉልህ ሰፍሯል። የኢስላም
አምልኳዊ ክንውኖች፣ ሕግጋትና ሥነ ምግባራዊ ደንቦች ሁሉ ይህ የተውሂድ ጥሪ በጉልህ ይንጸባረቅባቸዋል።
ኢስላም ለተውሒድ የሰጠውን ክብደትና ትኩረት ከሚያሳዩ ነገሮች አንዱ ተውሒድን መገለጫው፣ ከጣኦት አምልኮ፣
ከክርስትና፣ ከአይሁድም ሆነ ከሌሎች ሃይማኖቶች የሚለይበት አብይ ባህሪው ማድረጉ ነው። እናም የኢስላም
አብይ መገለጫ “አሐዳዊ እምነት” (ዲኑ ተውሒድ) የሚለው ቃል ሆነ። ኢስላም መሠረታዊ መልእክቱ በሁለት
ሐረጎች ይገለጻል። እነርሱን የተቀበለ ወደ ኢስላም ይገባል። የመጀመሪያው ሐረግ “ሸሃደቱ አን ላኢላሐ
ኢለላህ” "لا إله إلا الله" (ከሏላህ በስተቀር አምልኮት የሚገባው አምላክ እንደሌለ መመስከር)
ሲሆን ሁለተኛው “ወአነ ሙሐመደን ረሱሉላህ” "وان محمد رسول الله" (ሙሐመድ የአሏህ መልእክተኛ
መሆናቸውን መመስከር) ነው። የአሏህን አንድነትና የነቢዩ ሙሐመድን መልእክተኛነት መመስከር ናቸው። ከአሏህ
ሌላ አምላክ የለም ብሎ መመስከር ማለት ከርሱ ውጭ በሰማያትም ሆነ በምድር በእውነት የሚያመልኩት አምላክ
እንደሌለና ከርሱ ሌላ ያሉ አማልክት ሁሉ የሐሰት አማልክት መሆናቸውን መመስከር ነው። ይህ ምስክርነት
አሏህን ብቻ በፍጹም ቅንነትና ታማኝነት ማምለክንና ከርሱ ሌላ ያሉ አማልክትን ሁሉ ፈጽሞ አለማምለክን
ያካትታል። ሁለት ነገሮች እስካልተረጋገጠ ድረስም ጠቀሜታ አይኖረውም፡- አንደኛ፡- የአሏህን አሐዳዊነት
ከልብ አምኖ፣ አውቆ፣ እውነት ብሎና ወዶ መቀበል። ሁለተኛ፡- ከአሏህ ሌላ በሚመለኩ ነገሮች ሁሉ መካድ።
የአሏህን አንድነት በቃሉ መስክሮ ከአሏህ ውጭ የሚመለኩ አካላትን ያልካደና ያላስተባበለ ምስክርነቱ
አይፈይደውም። (انفي واثبات) የነቢዩ ሙሐመድን መልእክተኛነት መመስከር ማለት የታዘዙትን መፈጸም፣
ያስተላለፉትን መልእክት እውነት ብሎ መቀበል፣ ከከለከሉት መታቀብ፣ አሏህን እርሳቸው ባስተማሩት መንገድ
ብቻ ማምለክ፣ እርሳቸው ለሰው ልጆች ባጠቃላይ መላካቸውን ማወቅና ማመን፣ የአላህ አገልጋይ እንደሆኑ፣
እንደማይመለኩ፣ የማይስተባበሉና ሊታዘዟቸው የሚገቡ መልእክተኛ መሆናቸውን፣ የታዘዛቸው ጀነት፣ ያመጸባቸው
እሳት እንደተዘጋጀለት ማወቅና ማመን ነው። እንዲሁም በእምነትና አመለካከት፣ በአምልኮ ስርዓት፣ በሕግና
አስተዳደር፣ በስነ ምግባር፣ በቤተሰባዊ ጉዳዮች፣ በሐላልና በሐራም አጀንዳዎች ወዘተ የአላህን ሕግ
ከርሳቸው እንደምንቀበል ማወቅና ማመን ግድ ነው። ምክንያቱም የአሏህን መልእክት ለሰው ልጆች አድራሽ
ናቸውና። ተውሒድ አሏህ በባሮቹ ላይ ያለው መብት መሆኑና ከርሱ መዘናጋትና ችላ ማለት እንደማይገባ የአላህ
መልእክተኛው (صلى الله عليه وسلم) መግለጻቸው ከላይ ለሰፈረው ሃሳብ የበለጠ ጥንካሬ ይሰጠዋል።
ቡኻሪና ሙስሊም ባሰፈሩት ዘገባ ሙዓዝ ኢብኑ ጀበል እንዲህ ሲሉ አስተላልፈዋል፡- ከአሏህ መልእክተኛ
(صلى الله عليه وسلم) ጋር በአንዲት አህያ ላይ ነበርን። “ሙዓዝ ሆይ፣ አሏህ በባሮቹ ላይ ያለውን መብት፣ ባሮቹም
በርሱ ላይ ያላቸውን መብት ታውቃለህን?” አሉኝ። “አሏህና መልእክተኛው ያውቃሉ” አልኳቸው። “አሏህ
በባሮቹ ላይ ያለው መብት በርሱ ላይ ምንንም ነገር ሳያጋሩ በብቸኝነት ሊያመልኩት ሲሆን፣ ባሮቹ በርሱ ላይ
ያላቸው መብት ደግሞ በርሱ ላይ ምንንም ነገር ያላጋራን ሰው ላይቀጣ ነው።” አሉ። “የአሏህ መልእክተኛ
ሆይ፣ ለሰዎች ብስራት ልንገራቸውን?” አልኳቸው። “አታብስራቸው። እንዳይሳነፉ።” አሉ ። የዚህ መብት
ምስጢር አሏህ የሰውን ልጅ ካልነበረበት አስገኘው። ተቆጥረው ሊዘለቁ የማይችሉ ጸጋዎችንም ሰጠው። ፀሐይንና
ጨረቃን፣ ቀንና ሌሊትን ለርሱ አገልግሎት ይሰጥ ዘንድ ገራለት። አእምሮ ሰጠው። ሃሳብን የመግለጽ ችሎታን
አስተማረው። እናም ሲሳይን የለገሰ፣ ጸጋዎችን የሰጠ፣ አዛኝና ሩህሩህ አምላክ ሊመሰገን እንጅ ውለታው
ሊካድ አይገባም። ሊታወስ እንጅ ሊረሳ አይገባም። ሊታዘዙት እንጅ ሊያምጹት አይገባም። የቁርአን
የመጀመሪያው ኑዛዜ ይህን መብት መግለጽ ሆኗል። የአስር መብቶች አንቀጽ በመባል የሚታወቀው የቁርአን
አንቀጽ የሚጀምረው እንዲህ በማለት ነው፡-
وَاعْبُدُوا اللَّهَ وَلَا تُشْرِكُوا بِهِ شَيْئًا
وَبِالْوَالِدَيْنِ إِحْسَانًا وَبِذِي الْقُرْبَىٰ وَالْيَتَامَىٰ
وَالْمَسَاكِينِ وَالْجَارِ ذِي الْقُرْبَىٰ وَالْجَارِ الْجُنُبِ
وَالصَّاحِبِ بِالْجَنبِ وَابْنِ السَّبِيلِ وَمَا مَلَكَتْ
أَيْمَانُكُمْ إِنَّ اللَّهَ لَا يُحِبُّ مَن كَانَ مُخْتَالًا
فَخُورًا
“አላህንም ተገዙ። በእርሱም ምንንም አታጋሩ። በወላጆችና በቅርብ ዝምድና ባለቤትም፣ በየቲሞችም፣
በምስኪኖችም፣ በቅርብ ጎረቤትም፣ በሩቅ ጎረቤትም፣ በጎን ባልደረባም፣ በመንገደኛም፣ እጆቻችሁም ንብረት
ባደረጓቸው (ባሮች)፣ መልካምን (ሥሩ)፤ አላህ ኩራተኛ ጉረኛ የኾነን ሰው አይወድም።” (አን-ኒሳእ :
36)
በአል-አንዓም ምእራፍ ውስጥም የሰፈሩት አስሩ ኑዛዜዎች በዚህ መልእክት ተወጥነዋል፡-
قُلْ تَعَالَوْا أَتْلُ مَا حَرَّمَ رَبُّكُمْ عَلَيْكُمْ أَلَّا
تُشْرِكُوا بِهِ شَيْئًا وَبِالْوَالِدَيْنِ إِحْسَانًا وَلَا
تَقْتُلُوا أَوْلَادَكُم مِّنْ إِمْلَاقٍ نَّحْنُ نَرْزُقُكُمْ
وَإِيَّاهُمْ وَلَا تَقْرَبُوا الْفَوَاحِشَ مَا ظَهَرَ مِنْهَا
وَمَا بَطَنَ وَلَا تَقْتُلُوا النَّفْسَ الَّتِي حَرَّمَ اللَّهُ
إِلَّا بِالْحَقِّ ذَٰلِكُمْ وَصَّاكُم بِهِ لَعَلَّكُمْ
تَعْقِلُونَ
“ኑ፤ ጌታችሁ በእናንተ ላይ እርም ያደርገውን ነገር (በእርሱም ያዘዛችሁን) ላንብብላችሁ” በላቸው።
“በእርሱ (በአላህ) ምንንም ነገር አታጋሩ። ለወላጆችም በጎን ሥራ (ሥሩ)። ልጆቻችሁንም ከድህንት
(ፍራቻ) አትግደሉ። እኛ እናንተንም እነርሱንም እንመግባችኋለንና። መጥፎ ሥራዎችንም ከእርሷ የተገለጸውንም
የተደበቀውንም ሁሉ አትቅረቡ። ያችንም አላህ እርም ያደረጋትን ነፍስ በሕግ ቢኾን እንጅ አትግደሉ። ይህን
ታውቁ ዘንድ (አላህ) በእርሱ አዘዛችሁ።” (አል-አንአም : 151)
በአል-ኢስራእ ምእራፍ ውስጥ
የተካተቱት ኑዛዜዎችም እንደዚሁ ይህን መብት በመግለጽ ተወጥነዋል፡-
لَّا تَجْعَلْ مَعَ اللَّهِ إِلَٰهًا آخَرَ فَتَقْعُدَ مَذْمُومًا
مَّخْذُولًا وَقَضَىٰ رَبُّكَ أَلَّا تَعْبُدُوا إِلَّا إِيَّاهُ
وَبِالْوَالِدَيْنِ إِحْسَانًا إِمَّا يَبْلُغَنَّ عِندَكَ
الْكِبَرَ أَحَدُهُمَا أَوْ كِلَاهُمَا فَلَا تَقُل لَّهُمَا أُفٍّ
وَلَا تَنْهَرْهُمَا وَقُل لَّهُمَا قَوْلًا كَرِيمًا
“ከአሏህ ጋር ሌላን አምላክ አታድርግ የተወቀስክ ረዳት የሌለህ ትኾናለህና፤ ጌታህም (እንዲህ ሲል)
አዘዘ፡- እርሱን እንጂ ሌላን አትገዙ። በወላጆቻችሁም መልካምን ሥሩ። በአንተ ዘንድ ኾነው አንዳቸው ወይም
ሁለታቸው እርጅናን ቢደርሱ ፎህ አትበላቸው። አትገላምጣቸውም። ለእነርሱም መልካምን ቃል
ተናገራቸው።” (አል-ኢስራእ : 22-23)
ሙሐመድ የዐብደላህ ልጅ፣ የአብዱል ሙጦሊብ ልጅ፣ የሃሽም
ልጅ፣ የመናፍ ልጅ፣ የፈህር (ቁረይሽ) ልጅ፣ የማሊክ ልጅ፣ የነድር ልጅ፣ የኪናነህ ልጅ፣ የዐድናን ልጅ፣
የአሏህ ነብይ እስማዒል ልጅ፣ የአሏህ ወዳጅ የኢብራሂም ልጅ። አሏህ ከጥሩ ጎሳ መረጣቸው። የመሐይምነት
ዘመን ቆሻሻ ወደ ዘር ግንዳቸው አልገባም።
ሙስሊም እንደዘገቡት የአሏህ መልእክተኛ (صلى الله عليه
وسلم) እንዲህ ብለዋል፡- “አላህ ከእስማዒል ልጆች ኪናናን፣ ከኪናናህ ልጆች ውስጥም ቁረይሽን፣
ከቁረይሽ ሃሽምን፣ ከበኒ ሃሽም በኩል ደግሞ እኔን መርጧል።” (ሙስሊም ዘግበውታል)
አሏህ ነቢዩ ሙሐመድን (صلى الله عليه وسلم) ለሰው ልጆች
በታላቅ ስጦታነት አበረከተ። ይህም የሆነው ከአሏህ ዘንድ እጅግ የላቀ ክብር ስላላቸው ነው። ወዳጁን
ነቢዩን (صلى الله عليه وسلم) መታዘዝን እርሱን የመታዘዝ አካል፣ ከርሳቸው ጋር ቃል መጋባትን
ከርሱ ጋር ቃል መጋባት እንደሆነ ገለጸ። የርሱን ውዴታ ለማግኘትም ዋነኛው መስፈርት ነቢዩን (صلى الله
عليه وسلم) መከተል መሆኑንም አሳወቀ።
ተከታዮች የቁርአን አናቅጽ ይህን መልእክት ያዘሉ ናቸው፦
وَمَا أَرْسَلْنَاكَ إِلَّا رَحْمَةً لِّلْعَالَمِينَ
“(ሙሐመድ ሆይ!)
ለዓለማትም እዝነት አድርገን እንጅ አልላክንህም።” (አል አንቢያእ : 107)
مَّن يُطِعِ
الرَّسُولَ فَقَدْ أَطَاعَ اللَّهَ ۖ وَمَن تَوَلَّىٰ فَمَا
أَرْسَلْنَاكَ عَلَيْهِمْ حَفِيظًا
“መልክተኛውን የሚታዘዝ ሰው በእርግጥ አላህን
ታዘዘ። ከትእዛዝም የሸሸ ሰው (አያሳስብህ)። በእነሱ ላይ ጠባቂ አድርገን አልላክንህምና።” (አል ኒሣእ
: 80)
إِنَّ الَّذِينَ يُبَايِعُونَكَ إِنَّمَا يُبَايِعُونَ اللَّهَ
يَدُ اللَّهِ فَوْقَ أَيْدِيهِمْ ۚ فَمَن نَّكَثَ فَإِنَّمَا يَنكُثُ
عَلَىٰ نَفْسِهِ ۖ وَمَنْ أَوْفَىٰ بِمَا عَاهَدَ عَلَيْهُ اللَّهَ
فَسَيُؤْتِيهِ أَجْرًا عَظِيمًا
“እነዚያ ቃል ኪዳን የሚጋቡህ ቃል ኪዳን የሚጋቡት
አላህን ብቻ ነው። የአላህ እጅ (ኀይሉ) ከእጆቻቸው በላይ ነው። ያፈረሰም ሰው የሚያፈርሰው በነፍሱ ላይ
ብቻ ነው። በእርሱ ላይ አላህን ቃል ኪዳን የተጋባበትን የሞላም ሰው ታላቅ ምንዳን በእርግጥ ይሰጠዋል።”
(አል ፈትህ : 10)
قُلْ إِن كُنتُمْ تُحِبُّونَ اللَّهَ فَاتَّبِعُونِي
يُحْبِبْكُمُ اللَّهُ وَيَغْفِرْ لَكُمْ ذُنُوبَكُمْ ۗ وَاللَّهُ
غَفُورٌ رَّحِيمٌ
“በላቸው፡- «አላህን የምትወዱ እንደኾናችሁ ተከተሉኝ፤ አላህ ይወዳችኋልና።
ኀጢኣቶቻችሁንም ለናንተ ይምራልና። አላህም መሓሪ አዛኝ ነው።»” (አሊ ዒምራን : 31)
ምን አይነት አስተማሪ? ምን አይነት ሰው?…!
ምን አይነት ምስጢር ቢኖረው
ነው ከሰዎች የበላይ የሆኑ ሰዎችን ያመረተው?! ምን በተከበረ እጅ ወደ ሰማይ በዘረጋት ከዚያም
በእያንዳንዱ የእዝነት፤ የፀጋና፤ የመመራት በሮቿ በሰፊው የተከፈተችው?! ምን አይነት እምነት? ምን
አይነትስ ቁርጠኝነት? ምን አይነት ልፋት? ምን አይነት እውነት? ምን አይነት ወኔ? ምን አይነት ፍቅር?
ምን ቁምነገረኝነት!? ምን ለእውነት መታመን? ምን ፍጥረትን ማክበር?! የእርሱን ባንዲራ እስኪሸከምና
በስሙ እስኪናገር ድረስ አሏህ ከፀጋዎቹ ችሮታል። እንደውም የመጨረሻ መልእክተኛነትን ክብር እስካጠለቀ
ድረስ ፀጋዎቹን በርሱ ላይ አስፍኗል። በዚህም በሙሀመድ (صلى الله عليه وسلم) ላይ የአላህ ችሮታ ታላቅ ነበር።
የጎሳ አለቆችን ወደሚሰብኩት እምነት እንዲቸኩሉ ያደረጋቸው ምንድን ነው?! ለምንድን ነው አቡበከር፣
ጦልሃ፣ ዙበይር፣ ኡስማን፣ አበዱረህማን ቢን ዐውፍ፣ ሰዕድ ቢን አቢወቃስ እና ሌሎችም በታላቅ የኢማን
ፍጥነት ህዝቦቻቸው የቸሯቸውን ክብርና ድሎት ትተው በከባድ ችግርና በፍፁም ጭንቀት ወደተወጠረው አፍላው
ኢስላማዊ ህይወት የዞሩት?! ሙሐመድ ሰለላሁ ዓለይሂ ወሰለም በገንዘብና በአቅም ደካማ ሆነው ችግር፣
መከራና አስፈሪ አደጋዎች እየወረዱባቸው እራሳቸውንም ከአደጋ መጠበቅ ሳይችሉ… ደካሞች ግን ወደ እርሳቸው
ጥበቃ እንዲጠጉና ወዳነገቡት ባንዲራም እንዲሰበሰቡ ያደረጋቸው ምን ይሆን?! የጃሂሊያ ጉልበተኛው ዑመር
ኢብኑልኸጣብ አንገታቸውን በሰይፍ ሊቆርጥ ሄዶ ነበር። ነገር ግን በያዛት ሰይፍ ኢማን ክህደትን
የጨመረበትን የጠላታቸውን አንገት ወደ መቀንጠስ ያስዞረው ምን ይሆን?!… “ለነፍሴ ጥቅምንም ጉዳትንም
አልችልም፤ በእኔም ሆነ በናንተ ላይ የሚሰራውንም አላውቅም!” እያሏቸው በርሳቸው የሚያምኑ ሰዎች ግን
እንዲጨምሩ እንጂ እንዲቀንሱ ያልሆኑት ለምንድን ነው?!… ምድር ከየአቅጣጫዎቿ እንደምትከፈትላቸውና
እግሮቻቸው የአለምን የሀብትና የዘውድ ማማ እንደምትረግጥ… እልቅናንና ክብረትንም እንደምትሸለም… ተደብቀው
የሚያነቡት ቁርኣንን በአለም… (በህዝቦቻቸው ላይ ብቻ ሳይሆን… በደሴታቸውም ብቻ ሳይሆን…) መልዕክቱ
ለሚመለከተው የሰው ዘር ሁሉ እንደሚያነቡትና እንደሚያስተምሩት፤ በየዘመኑና በየቦታው ሰዎች ከፍ ባለ ድምጽ
እንደሚያነቡት ሲነገሯቸው እንዴት አመኑ!?… የሚደንቀው! ወደፊትና ወደኋላቸው፣ ወደ ቀኝና ወደ ግራቸው
ሲዞሩ ህይወታቸው ችግር፣ ጥበት፣ ጭንቀት፣ ረሀብ፣ ስቃይና ሰቆቃ ሆኖ ይህን መልእከተኛቸው የሚነግሯቸውን
ትንቢት እንዲያምኑ ያደረጋቸው ምን ይሆን?!… ምንድን ነው ልባቸውን የቂንና ቁርጠኝነት የሞላው?!…
እርሳቸው የዐብደላህ ልጅ “ሙሐመድ” ሰለላሁ ዓለይሂ ወሰለም ናቸው! ከእርሳቸው ውጪ እንደዚህ ያለ ማን
አለ?!… ህዝቦቻቸው ታላቁን ስብእናቸውንና ታላቅነታቸውን በዐይናቸው ተመልክተዋል። ንጽህናቸውን፣
ጥብቅነታቸውን፣ አደራ ጠባቂነታቸውን፣ ጽናታቸውንና ጀግንነታቸውን በዓይናቸው አይተዋል። እዝነታቸውንና
ፍቅራቸውን አስተውለዋል፤ አስተዋይነታቸውንና ግልጽነታቸውን ተመልክተዋል። ሙሐመድ ሰለላሁ ዓለይሂ
ወሰለም የቀን ራዕያቸውንና የማታ ፍካሬያቸውን በሚያፈሱባት ጊዜ የህይወትን ስፋት ህይወት በደረሰበት ሁሉ
ሲጓዝ አዳመጡ! ይህን ሁሉ ተመለከቱ፤ ከዚህም ሌላ የማይቆጠር ብዙ የሚደንቅን ነገር..! ልጅነታቸው
አንደሌሎች ልጆች አልነበረም። ከህፃናት የዛዛታ ቦታ ወደ ጎልማሶች ቁምነገረኝነት በማዘንበሏ የሰዎችን ልብ
የሳበች ህፃንነት። ወደ ጨዋታ የተጠሩ ጊዜ “እኔ ለዚህ አልተፈጠርኩም!” ይሉ እንደነበር ተዘግቧል።…
ወጣትነታቸውማ ምን ያማረ ወጣትነት?!… የህዝቦቻቸው መነጋገሪያ ነበሩ። በጣም የሚደንቁ፣ የተከበሩና
የተወደዱ።… በጉልምስናዎማ የሁሉንም አይን ጆሮና ልብ የሞሉ ፍፁም ፅድቅ ነበሩ። በሚዛናዊ ልቦና እነዚያ ሙእሚኖች የአላህን ብርሃን በአይናቸው አይተው
ተከተሉት። በእርግጥም ሚዛናዊ እንዲሆኑ የረዳቸውን ንፁህ ልባቸውን አሏህ መልእክተኛውን ባለድል በሚያደርግ
ጊዜ ያመሰግኑታል። ደሴቱ ሁሉ ለእርሱ ሆኖ ሳለ የዱንያ ጥላቻና የአላህ ፈራቻ እንጂ ሌላን ሳይጨምር፤
ሰንበሌጥ ላይ ተኝቶ የሰንበሌጡ ምስል ሰውነቱ ላይ ሲሳል፤ ከዚህ ሁኔታውም ሳይቀየር ጌታውን የተገናኘ ጊዜ
ሲገናኝ… ያኔ ልባቸውን ያፈቅሩታል። ሚዛናዊ እይታውንም ያወድሱለታል። ባንዲራው አለምን የሞላ መሪና
የተከበረ የአሏህ መልእክተኛ ሆነው ሳለ ሚንበር ላይ ሲወጡ እያለቀሱና “ያለአግባብ ጀርባውን የገረፍኩት
ሰው ካለ ይኸው ጀርባዬን ይበቀለኝ! ገንዘቡን ያላግባብ የወሰድኩበት ካለ ይኸው ገንዘቤን ይቀበለኝ!”
እያሉ ሲጣሩ ባዩዋቸው ጊዜ… የሰዎችን ችግርና ረሃብ መቋደስ ብቻ ሳይሆን እራሳቸውና ቤተሰባቸው የችግሮች
ዋና ገፈት ቀማሽ ሆነው ሰዎች ሲራቡ የመጀመሪያዎቹ ራብተኞች፤ ሰዎች ሲጠግቡም የመጨረሻዎቹ ጠጋቢዎች ሆነው
ባዩዋቸው ጊዜ… በእርግጥም ወደ ኢስላም ጐዳና ለመራቸው ጌታ ምስጋናን ከመጨመር በኋላ ነገርን በንጽህናና
በሚዛናዊነት አንዲያስተውሉ ላደረጋቸው አስተዋይ ልቦናቸው ያላቸው ክብር ይጨምራል። “ሰዎች ሆይ እኔ
ወደናንተ የተላኩ የአሏህ መልክተኛ ነኝ!” ባሉ ጊዜ ለእውነተኝነታቸው ምርጥ ምስክር የሚሆነውን ታላቅ
ህይወት ይመለከቱታል!? ይች ህይወት በፅድቅነቷና በታላቅነቷ የምርጡን አስተማሪና የቸሩን መልእክተኛ
እውነተኛነት ትመሰክራለች። እኔ የአሏህ መልዕክተኛ ነኝ ሊሉም ይገባቸዋል!… የመጨረሻው የለሊቱ ክፍል
በሚገባ ጊዜ ከእንቅልፍ ቀጥ ብለው ይቆማሉ። ውዱእም አድርገው ወዳስለመዱት ጌታዉን ወደማናገርና ወደማልቀስ
ይዞራሉ። ይሰግዳሉ፤ ያለቅሳሉ። አገሩ ሁሉ ለጥሪያቸው በተገዛ ጊዜ… የምድር ነገስታትም ወደርሳቸው
መልእክት ጌታቸውን የፈሩና ለግርማቸው የተናነሱ ሲሆኑ በዞሩ ጊዜ… ቅንጣት ኩራትና እራስ ወዳድነት
አላለፈችባቸውም። ሀብትን፣ ስልጣንን፣ ክብርንና ተሰሚነትን ታሳቢ ሳያደርግ የጌታቸውን ትእዛዝ የሚፈጽሙና
የሚያስተላልፉ ነበሩ። ይኸው እኚህ ናቸው የሰው ልጆች መምህር የነብያት መደምደሚያ፤ ይኸው እኚህ ናቸው
የልባችን መድሃኒት፣ የመንገዳችን ብርሃን፤ በመመሪያቸው እንኖራለን! በፍቅራቸው ልባችንን እናበራለን!
ፈለጋቸውን እንከተላለን! የርሳቸውን ልፋት ለፍተን እረፍታቸውን እናርፋለን!!! ባላችሁ እውቀት እና ጥበብ
ህይወቱን መርምሩት፤ ፈትሹት!… ስህተትን ተመለከታችሁን!? ጥመትን አያችሁን!? አንዴም ቢሆን ዋሽቷልን!?
አንዴም ቢሆን ከድቷል!? አንዴም ቢሆን ሰውን አዋርዷል!? ሰውን በድሏል!? ቃልን አፍርሷል!? ዝምድናን
ቆርጧል!? የሰውን ገንዘብ በልቷል!? ከመልካም ባህሪያት ተራቁቷል!? አንድን ሰው ሰድቧል!? ጣኦት
አምልኳል?ይህ ሁሉ ይህ ንፁህ ስብእና ውስጥ የለም። ህይወቱን በደንብ ፈትሹ! ተመራመሩት! አንዲት
ግርዶሽም ሽፋንም የለውም። ህይወቱ ግልጽ ነው ምስጢርም የለውም።