about-us

about us

የእስልምና ሀይማኖት የሰው ልጆችን በዘር፣ በጎሳ፣ በቀለም ፣ በፆታ የማይለይ በፈጣሪያቸው ዘንድ የማበላለጫው ብቸኛው መስፈርት ተቅዋ ወይንም አላህን መፍራት ብቻ አድርጎ ያስቀመጠ ድንቅ ዕምነት ነው። ይህ እጅግ ጥልቅ የሆነ መልዕክት የያዘ ሀሳብ ሲሆን ከዚህም ውስጥ አንዱን ሰበዝ ብቻ መዘዝ አድርገን ባጭሩ ብንመለከት የሴቶችን ደረጃ፣ መብት እና ክብር ከፍ ያደረገ፤በማህበረሠቡ ውስጥ የላቀ ማንነትን  ያጎናፀፈ፤ ከውልደቷ፣ እድገቷ፣ትምህርቷ፣ትዳሯን እና እናትነቷን እንዲሁም በውርስ ከለላን በማግኘት ላይ ጥልቅ የሆነ ሽፋንን አስቀምጦላታል። የኢስላም ጠላቶች እና አላዋቂዎች "ሴት ልጅ ሰው ናት ወይንስ አይደለችም?" የሚል ሀገር አቀፍ ስብሠባዎችን እስከማካሄድ የደረሰ ውርደትን ያዋረዷት ጊዜ ያለፈ ቢሆንም በእኩልነት  እና ዘመናዊነት ሠበብ ደግሞ አሁን የምናየውን ዘመናዊ ባርነት እያላበሷት ይገኛሉ። አሳዛኙ ጉዳይ ግን ይህንን የገቡበት ጉድጒድ የመግባት ጭፍን አባዜን ተከትለን ከሚያራግቡት ውስጥ ግንባር ቀደሞቹ እኛው ሙስሊሞቹ መሆናችን ነው። ኢሕሳን መድረሳ በ2005 ዓ.ል በአምስት ተማሪዎች ሲቋቋም ከላይ በቁንጽል ያየነውን ሸሪዓ በቀኝ እና በግራ እየሄድን ያለበትን የሴቶች ከፍተኛ የእውቀት ማነስና የተግባር ጥፋቶችን ለማረም በማቀድ ሴቶችን በኢስላማዊ እውቀት የማነጽ አላማን ሰንቆ የተነሳ ነው። በዚህም ዛሬ ላይ ለዘጠነኛው ጊዜ ሲያስመርቅ በሂደቱ ራሳቸውን በተለያዩ ሸሪዓዊ፣ ማህበራዊ፣ የትዳር፣ የልጅ አስተዳደግ እና የተለያዩ ውይይቶችን በማካሄድ እውቀታቸውን ከማዳበራቸው በተጨማሪ አራት ተማሪዎችን ለኡስታዛነት በማብቃት እዚሁ መድረሳ ውስጥ አገልግሎት መስጠት ጀምረዋል። በመድረሳው ውስጥም የፊቅህ፣ የአቂዳና የሀዲስ ትምህርቶችን የሚሰጡ ሲሆን ከዚህ በዘለለም የሸሪዓ አስተምህሮትን ወደ ህይወታቸው በተጨባጭ የሚያመጡበትን ሰፋፊ የአቅጣጫ ጥቆማዎችንና የልምድ ልውውጦችን ያካሂዳሉ።

ተልዕኮ

"የእኛ ተልዕኮ ሴቶች የሸሪዓን ትምህርት በማጥናትና በመረዳት በንቃት የሚሳተፉበት፣ ጠቃሚ እውቀት ቀስመው ማንነታቸውን ሚያንፁበት እና ስለ ልጆች አስተዳደግና በሌሎች መሀበረሰባዊ ዘርፎች ስልጠና የሚወስዱበት ሁሉን አቀፍ ቦታ መፍጠር ነው።
ሴቶችን በእውቀት ማብቃት እና አስፈላጊውን ግብአት እና ድጋፍ በማድረግ ስለ ኢስላማዊ መርህ እውቀት እና ጥልቅ ግንዛቤ እንዲኖራቸው ማድረግ ነው። በሕይወታቸው ውስጥ
ተፈጻሚነት ያለው ወሳኝ አስተሳሰብን ፣ ምሁራዊ ንግግርን እና ጠንካራ ሴት መሪዎችን ለማዳበር በትምህርት እና የላቀ ችሎታ እንዲኖራቸው ማድረግ ነው።

ራዕይ

ኢንሻአላህ ራዕያችን ሴቶች እኩል የሸሪዓ ትምህርት የሚያገኙበት ማህበረሰብ መፍጠር ነው። ይህም ሁሉን አቀፍ የትምህርት ተቋማትን ማቋቋም፣ ሴት ምሁራንን ማብቃት፣ ግንዛቤን ማሳደግ እና መካሪና ድጋፍ መስጠትን ይጨምራል። ይህንን ራዕይ እውን ለማድረግ በጋራ እንስራ