ጥቂት ስለ እውቀት

"እውቀትን ፍለጋ የወጣ ሰው ወደቤቱ እስኪመለስ ድረስ
በአላህ መንገድ (ጂሀድ) ላይ ነው" ረሱል(صلى الله عليه وسلم)

"የተማረ ሰው ማለት መሀይምነቱን መቀነስ የጀመረ አንጂ
ከመሀይምነቱ ነፃ የወጣ ማለት አይደለም" አቡ መህዲ

"ልጅህን ቁርአን አስተምረው ፡፡
ቁርአን ሁሉንም ነገር ያስተምረዋል" ሰለፎች

"ትምህርት በደስታ ዘመን ውበት ፣ በመከራ ዘመን መጠለያ ፣
በእርጅና ዘመን ምርኩዝ ነው" ኢብን ሙባረክ

"የሰው ልጅ የአእምሮውን አቅጣጫ እስካልለወጠ ድረስ
ህይወቱ ሊለወጥ አይችልም"ረዋዒኡን ሚነል ፊከር

''''' እውቀት
ከተግባርና ከንግግር በፊት
ይቀደማል!! '''''

እውቀትን በመፈለግ ሂደት ውስጥ ጥንቃቄ ልናደርግባቸው ከሚገቡ ጉዳዬች ውስጥ ሁለቱን እንመልከት:-

ኢኽላስ:-  እውቀት ፈላጊ የሆነ ሰው መዳረሻው የአላህን() ፊት መከጀልና የመጨረሻውን ሀገር ማሳመር መሆን ይገባዋል። ከይዩልኝ ይስሙልኝ እጅግ መጠንቀቅ ያስፈልጋል። የአላህ መልእክተኛ እንዲህ ይሉናል።
مَنْ طَلَبَ الْعِلْمَ لِيُجَارِيَ بِهِ الْعُلَمَاءَ أَوْ لِيُمَارِيَ بِهِ السُّفَهَاءَ أَوْ يَصْرِفَ بِهِ وُجُوهَ النَّاسِ إِلَيْهِ أَدْخَلَهُ اللَّهُ النَّارَ .
رواه النسائي وحسنه الألباني في صحيح
"ከሊቃውንት ለመወዳደር ወይም ከሞኞች ለመሟገት ወይም የሰዎችን ትኩረት ወደርሱ ለማዞር ብሎ እውቀትን የሚፈልግ አላህ() እሳት ያስገባዋል።" ከውጭም ሆነ ከውስጥ ከትልቅም ሆነ ትንሽ ሪያእ ንጹህ መሆንን አደራ! ባወቀው ነገር መስራት:-  ከእውቀት ፍሬዎች አንዱ ባወቀው ነገር መስራት ነው። ያወቀና የማይሰራበትን ሰው ከየሁዳዎች የተመሳሰለ ሲሆን ይህንንም አላህ() በቁርአን እንዲህ ሲል ገልፆታል።
مَثَلُ الَّذِينَ حُمِّلُوا التَّوْرَاةَ ثُمَّ لَمْ يَحْمِلُوهَا كَمَثَلِ الْحِمَارِ يَحْمِلُ أَسْفَارًا بِئْسَ مَثَلُ القوم الذِينَ كَذَّبُوا بِآيَاتِ الله وَاللَّهُ لَا يَهْدِي الْقَوْمَ الظَّالِمِينَ
" የእነዚያ ተውራትን የተጫኑትና ከዚያም ያልተሸከሟት ( ያልሠሩባት ) ሰዎች ምሳሌ መጽሐፎችን እንደሚሸከም አህያ ብጤ ነው ፡፡ የእነዚያ በአላህ አንቀጾች ያስተባበሉት ሕዝቦች ምሳሌ ከፋ ፡፡ አላህም በዳዮችን ሕዝቦች አይመራም ፡፡ "
እንዲሁም ያለ እውቀት መስራትንም ከነሳራዎች ጋር መመሳሰላቸውን በሱረቱል ፋቲሀ ላይ እንደተገለፁት የጠመሙት ቢጤ ነው።

''''' 📚"ዒልም ማለት
አላህን መፍራት ነው!"
አል-ኢማሙ ማሊክ '''''



መልእክተ ኢሕሳን


አላህ (ሱ.ወ) የሰውን ልጅ ከፈጠራቸው ታላላቅ ፍጡራን ሁሉ የበላይ አድርጎ ክብርን ያጎናፀፈው ድንቅ የሆነ አካል በውስጡ በማድረጉ ሲሆን ይህንን አፈጣጠሩ ሲተነተን እጅግ ገራሚ የሆነውን አካሉን በአግባቡ ያለመጠቀሙ ደግሞ የተሰጠውን ክብርና ደረጃ አውጥቶ በመፈጥፈጥ እጅግ ካነሱት ፍጡራን ከእንስሳ በታች እንደሚወርድ በቅዱስ ቁርአኑ ያሳውቀናል፡፡
አእምሮ !!! አእምሮ ይማራል፤ ያድጋል፤ ይበለፅጋል፤ ያስባል፣ ይለወጣል፤ ጥሩና መጥፎን ይለያል። ታላላቅ ስብእናዎችን ይፈጥራል፡፡ ለግለሰብ ለቤተሰብ፣ ለማህበረሰብ ብሎም ለአለም ሊተርፍ የሚችሉ ግሩም ሀሳቦችን ያመነጫል። ወደ ተግባር እንዲቀየርም ያደርጋል። የዛኔ የተሰጠውን የምድር ከሊፋነት ተግባር ይወጣና "...የሰውን ልጅ አላቅነው … " የተባለለትን የክብር ደረጃ ይጎናፀፋል ። በአንፃሩ ከተሄደ ተቃራኒውን ያስወርሳል፡፡ ይህ ታዲያ የግለሰቡ ምርጫ መሆኑ ነው አሳሳቢው ጉዳይ!።
የአላህ (ሱ.ወ) ተውፊቅ ሆኖ የእስልምናን እውቀት የማሽተት እድሉ የገጠመው ሰው ታዲያ የሚለይበት አንዱ ጉዳይ ይህ ነው፡፡ ዲኑን ያወቀ ሰው ለውጡ ከአልባሳት መዝለል አለበት፡፡ አንደበቱ ፣ አስተያየቱ ፣ ሀሳቦቹ ባጠቃላይ ኑሮው እነዚህ የዲን አስተምህሮቶች ሊንፀባረቁበትና ህይወቱ አድርጎ ዲኑን ሊኖረው ይገባል፡፡ የተማራችሁትን መለስ ብሎ ማየት፣ እያንዳንዱን እውቀት ወደ ህይወትና ወደ ተግባር መለወጥ፣ የእውቀት ሰብሳቢ ከመሆን የተግባር ሰው ወደ መሆን ተሯሯጡ፡፡
በእውቀታችሁ ተጠያቂ የምትሆኑበት ቀን አለና ዛሬ ወደ ተግባር ቀይራችሁ ተጠቃሚ ሁኑ።

አሏሁ (ሱብሐነሁ-ወተዐላ) ለባርያዎቹ በምድር ላይ ከለገሳቸው ጸጋዎች አንዱ እና ታላቁ ዒልም (እውቀት) ነው። ከእውቀትም አሏህን (ሱብሐነሁ-ወተዐላ) የምናውቅበት የዲን እውቀት፣ ታድያ ይህን ታላቅ ስጦታ ለማግኘት እድሉ የተመቻቸላቸው ሰዎች ዋጋውን ለመገንዘብ፣ እሱን በደንብ ለመረዳት፣ ለመተግበር እና ለሌሎች ለማስተላለፍ ጠንካራ፣ ትጉ፣ አላማውን ያወቀ ሰው ሆኖ መገኘት፣ በመንገዱ ላይ የሚያጋጥመውን ችግር ተቋቁሞና አስፈላጊውን መስዋእትነት ከፍሎ ውጤታማ ለመሆን ቆራጥ መሆንን ይጠይቃል።
ስኬታማ ሰው ማለት በየትኛውም የህይወት ክፍሉ ጉዳዮች ተመቻችተውለት የሚማርና የሚሰራ ሳይሆን ከአስቸጋሪ ውጣ ውረዶች መሃል አላማውን በጽናት ይዞ የሚጓዝና ቁልቁለቱን ወርዶ ዳገት ሳያደክመው ከከፍታ ማማ ላይ ከውጤት ጋር ብቅ የሚል ጀግና ነው።
ከራሱ ጋር በኑሮ ውጣ ውረድ እየተንገላታ የዒልምን ማዕድ ለመቋደስ የሚታትር ተማሪ አውቆም ሆነ በዝንጋቴ ወይንም በማህበረሰቡ ዘንድ ለኢስላማዊ እውቀት እና ለመምህራን ከተሰጠው አነስተኛ ግምት በመነሳት የመሰል ተማሪዎችንም ሆነ የመምህሩን (የኡስታዙን) ሞራል የሚነካ ተግባሮችን ባለመፈጸም ከብዙሃን ተመርጦ ለእርሱ የተሰጠውን የጌታውን ኒዕማ በማጣጣም በዱንያም በአኺራም የተሻለ ቦታ የማግኘት እድሉን እንዲያሰፋ አደራ እላለሁ።

"አላህን ከባሪያዎቹ መካከል የሚፈሩት አዋቂዎቹ ናቸው" ይለናል ታላቁ የሰው ልጆች የህይወት መመሪያ የሆነው ቅዱስ ቁርአን። የተፈጠርንበትና በዚህች ምድር ላይ የተተኪነትን ደረጃ በማጎናፀፍ ከመላእክት በላይ ደረጃ የተሰጠን ለጨዋታና ለዛዛታ እንዳልሆነም ያሳውቀናል። ይሀንን አላማቸውን የተረዱና የተገበሩም በመጨረሻው አለም የፈለጉትን የሚያገኙና ከሚፈሩትም የተጠበቁ ናቸው። የነሱ የእገዛ መሳሪያቸውም ትክክለኛ እውቀት ነው። እያንዳንዱ ሰውም ጌታውን ያውቀውና ይገዛው ዘንድ ትክክለኛውን እውቀት መፈለግና መተግበር የነፍስ ወከፍ ግዴታው ነው፡፡ የነብያት ወራሽ የሆኑትን ኡለሞች ማክበርና ማላቅ አጅግ አስፈላጊና የተገባ ነው። የእውቀት ፈላጊ ስነምግባሮችን ማወቅና መተግበር ያስፈልጋል። የእውቀትን ታላቅነት መረዳትም ከስኬት ያበቃል። ለዚህም በንቃትና በትኩረት መንቀሳቀስና በዱዐ በመታገዝ ከስኬት ትበቁ ዘንድ አደራ አላለሁ፡፡

ኢሕሳን الإحسان

ቡኻሪና ሙስሊም ባሰፈሩት ዘገባ ሙዓዝ ኢብኑ ጀበል እንዲህ ሲሉ አስተላልፈዋል፡-
ከአላህ መልእክተኛ (صلى الله عليه وسلم) ጋር በአንዲት አህያ ላይ ነበርን። “ሙዓዝ ሆይ፣ አላህ በባሮቹ ላይ ያለውን መብት፣ ባሮቹም በርሱ ላይ ያላቸውን መብት ታውቃለህን?” አሉኝ። “አላህና መልእክተኛው ያውቃሉ” አልኳቸው። “አላህ በባሮቹ ላይ ያለው መብት በርሱ ላይ ምንንም ነገር ሳያጋሩ በብቸኝነት ሊያመልኩት ሲሆን፣ ባሮቹ በርሱ ላይ ያላቸው መብት ደግሞ በርሱ ላይ ምንንም ነገር ያላጋራን ሰው ላይቀጣ ነው።” አሉ። “የአላህ መልእክተኛ ሆይ፣ ለሰዎች ብስራት ልንገራቸውን?” አልኳቸው። “አታብስራቸው። እንዳይሳነፉ።” አሉ ።

የፍጥረቱ አለም አላማ ምንድነው?

አምላካችን አሏህ እንዲህ ይላል:-

«وَمَا خَلَقْتُ الْجِنَّ وَالْإِنسَ إِلَّا لِيَعْبُدُونِ»
«ጋኔንንና ሰውን ሊገዙኝ እንጅ ለሌላ አልፈጠርኳቸውም::»
[ሱረቱ-አዝ-ዛሪያት:56]

«يَا أَيُّهَا الَّذِينَ آمَنُوا ارْكَعُوا وَاسْجُدُوا وَاعْبُدُوا رَبَّكُمْ وَافْعَلُوا الْخَيْرَ لَعَلَّكُمْ تُفْلِحُونَ ۩»
« እናንተ ያመናችሁ ስዎች ሆይ (በስግደታችሁ) አጎንብሱ፣ በግንባራችሁም ተደፉ፣ ጌታችሁንም ተገዙ፤ በጎንም ነገር ሥሩ፤ ልትድኑ ይከጃልላችኋልና::»
[ሱረቱ-አል-ሐጅ:77]

ዱንያ እኔን ስታጣ

እልል በሉ ተብሎ ገንፎ ተገንፍቶ
የዘጠኝ ወር ስቃይ ሸክሙ ተቃሎ
እሰይ እንኳን መጣሽ በሉ ስም አውጡላት
አድገሽ ተመንደጊ ቀጥይ ወደ ትምህርት
በመልካም ገበታ በፍቅር በፍቅር አድጌ
ከቁርአን ከሐዲስ ሁሉን ተመግቤ
ብቁ ሰው ተብዬ በሃብትም አብቤ
ወልጄ ከብጄ ልጆቼንም ድሬ
በዘመን ከፍታ እድሜዬን ሳየው ዞሬ
ለትውልድ ጠቃሚ ቁም ነገር ሳልሰራ
በስራ በኑሮ ህይወት ተወጥራ
ይሄ ነው የሚባል ቢጨመቅ የማይወርድ
የእድሜ ዘመን ቁጥር ሚዛን ላይ የማይከብድ
ተራ አርቲቡርቲ የወሬ ጋጋታ
በሆነ ብልጭልጭ ህይወቴ ተሞልታ
በስተመጨረሻ ባለቀው ዘመኔ
ከማለት በስተቀር አይ እኔ አይ እኔ
ጣጣዬን ጨልሼ ባዶዬን ስወጣ
ምን ይጎድላት ይሆን ዱንያ እኔን ስታጣ!!

ዘመናት አለቁ ቀኑ ተቃረበ

ዘመናት አለቁ ቀኑ ተቃረበ
የጊዜም በረካ መጣ እየጠበበ
አማናም ተነሳ የሚታመን ጠፋ
እውነትም አነሰ ሀሰትም ተስፋፋ
ወንዞችም ደረቁ ፎቆችም አደጉ
እናቶች ጌታቸውን ወለዱ አሳደጉ
ፀጉሮች ተቆለሉ ገንዘቦች ዳበሩ
ግድያም በርክቶ ስልጣኖች ከረሩ
አላዋቂም በዛ ኡለሞች አለቁ
ፍርድም ተዛነፈ ሀቀኞች አፈሩ
ይህን ሰአት ጠብቅ ከደረስክ አደራ
አሉ ያላህ ነብይ ከደረሰህ ተራ
ጠንቀቅ በል አስተውል ሱናዬን በጥርስህ
ነክሰህ መያዙ ነው ነጃ የሚያወጣህ
በእውቀት በተቅዋ ያልተያዘ ለታ
እንደ ባህር አረፋ ሲገፋ ሲምታታ
ከወጣው ሲወጣ ከወጣው ሲወጣ
አይቀሬው ሞት መጥቶ ተጨንቃ ስትወጣ
ወይኔ ከሳራዬ .......መልሱኝ ሲመጣ
ማን ይሰማ ይሆን የከሳሪን ጣጣ??!!!!

አንቺ ውድ እህቴ

አሥ-ሠላሙ ዐለይኩም አንቺ ውድ እህቴ፤ እኔ እወድሻለሁ ከልቤ ከአንጀቴ
ዝምድና ባይኖረን ወይም ጉርብትና፤ ጠባብ ባልሆነው በሰፊው ጎዳና
ተገናኘን እቴ፤ በእስልምና።
ምንም እንዃን ባላይሽም በአይኔ፤ ስለአገኘሁሽ በኢስላም በዲኔ
ከምንም በላይ፤ ደስ ብሎኛል እኔ።
አንቺ ውድ እህቴ እኔ እወድሻለሁ፤ በአኺራ ጀነትን እመኝልሻለሁ።
አንቺ ውድ እህቴ ልንገርሽ አደራ፤ የትም ቦታ ብንሆን አሏህን እንፍራ
ለነገ ስንቃችን መልካምን እንስራ፤ መሄዳችን አይቀር መቼም፤ ወደ አኺራ።
በርቺልኝ እህቴ፤ ፍቅርሽን ሳስበው አልቻለም አንጀቴ
ተንሰፈሰፈልሽ መላው አካላቴ፤ እኔ እወድሻለሁ እስከ እለቴ ሞቴ
በሰላም ኑሩልኝ ውድ የአኺራ እህቴ!!

ውዷ__እህቴ!
ውበትሽ ሀያዕ ነው!
ፍካትሽ ኢስላም ነው!
ድምቀትሽ ዒማን ነው!
የቁንጂናሽ ሚስጥር በሂጃብሽ ስር ነው!!!

የማስተዋል ግብዣ 1

አንድ ሰው ወደ ኢማሙ አህመድ ኢብኑ ሃንበል ዘንድ በመምጣት እንዲህ ሲል ይጠይቃቸዋል፡-
ጠያቂው፡- አንቱ ኢማሙ አህመድ ሆይ! ከሰዎች ሰላም የምሆንበት መንገድ እንዴት ነውን?
ኢማሙ አህመድ እንዲህ አሉት ፡ ያንተን ትሰጣቸውና - የእነሱን ያልተቀበልክ እንደሆን ፣
እነሱ አንተን እያስቸገሩህ - አንተ ደግሞ የማታስቸግራቸው ከሆነ ፣
አንተ የእነሱን ጉዳዮች እየፈፀምክላቸው - እነሱ ደግሞ ያንተን ጉዳይ እንዲፈፅሙልህ የምታስገድዳቸው ካልሆንክ ... ከእነሱ ሰላም መሆን ትችላለህ ይሉታል ፡
ከዚያ ሰውዬው እንዲህ አላቸው ፡ አንቱ ኢማሙ አህመድ ሆይ ! ይሄን ማድረግ እጅጉን ይከብዳል'ኮ!!
ከዚያም እርሳቸው እንዲህ አሉት ፡ እስኪ ዝም በል ! ይሄንንም ሁሉ አድርገህ ከእነሱ ሰላም በሆንክ!! ምንጭ፡- ሲየር አዕላሙ ኑበላዕ ( 11-12 )

የማስተዋል ግብዣ 2

አንዲት ሴት ወደ ታዋቂው ዳኛ ሸዕቢይ ዘንድ በመሄድ ባሏን ከሰሰች።
ክሷን ስታቀርብም በለቅሶ ታጅባ ነበር። ዳኛው በለቅሶዋ ስሜቱ በመነካቱ ተከሳሽ ወደሆነው ባሏ ዘወር ብሎ " ይህች ሴት በጣም የተበደለች ይመስለኛል " አለው ።
ባሏም " የነቢዩላህ ዩሱፍ ወንድሞችም በምሽት ወደ አባታቸው ዘንድ ሲመለሱ እያለቀሱ ነበር ። ነገር ግን ተበዳዮች ሳይሆኑ በዳይ ነበሩ ።

የማስተዋል ግብዣ 3

የአእምሮን እድገት ከሚጨምሩ ነገሮች ውስጥ አንድና ዋነኛው አስተዋይ መሆን ነው። ያየውን ሁሉ የሚናገር ህጻን ልጅ፣ የሰማውን ሁሉ የሚያወራ ውሸታም፣ የተመኘውን ሁሉ የሚጠብቅ ሞኝ ነው። ያልታረሰ መሬት ላይ የተዘራ ዘር በአረም ይዋጣል። ሳያረጋግጥ የሚያወራ ጥርጣሬ ህሊናውን ይጎረብጠዋል። አንድ አይኑን አጥቶ ሲያለቅስ ያየኸው ሰው ሁለት አይን አጥፍቶ ሊሄን ይችላል። እጁ ተቆርጦ ያየኸው ሰው ገሎ ሊሆን ይችላል። ለማረጋገጥ መረጃ፣ ላለመታለል መጠንቀቅ፣ ላለመጠርጠር አጢኖ ማስተዋል ያስፈልጋል።

መራር እውነታዎች

1

ዶክተር ገርቢያ አልገርቢ ትባላለች። በሙያዋ ዶክተር ናት። እንዲህ ስትል አስተዋዮችን ታናግራለች፦
"እጅግ አደገኛ እና ውስብስብ የሆኑ ቀዶ ጥገናዎች በሰው ልጅ ወሳኝ ክፍሎች ላይ ይካሄዳሉ። በአእምሮውና በልቡ ላይ። ህይወቱ ባጠቃላይ በነዚህ ክፍሎቹ ላይ የተንጠለጠለ ነው።
-ይህን ቀዶ ጥገና የሚያካሂደው ሰፋፊ አልባሳት የለበሱ ፣ እራሳቸውን የሸፈኑ ፣ የፊት መሸፈኛ የለበሱ ፣ የእጅ ጓንቶችም ያጠለቁ ሰዎች ያሉበት የህክምና ቡድን ነው። ይህ አለባበሳቸው ግን ለዚህ ውስብስብና አደገኛ ስራ እንቅፋት አልሆነባቸውም።
-ከዚያ ግን "ሒጃብና ኒቃብ ስራን ፣እድገትንና ስልጣኔን ከሚያደናቅፉ እንቅፋቶች ውስጥ ናቸው' የሚል ሰው ታያለህ!!"

2

እናት፡ ብሩን የት እንደምደብቀው አላውቅም ልጄ ሁሉም ቦታ ብደብቀው ያገኘዋል ። ጎረቤት፡ መፅሀፍ ውስጥ ደብቂው እዛ ከሆነ መቼም አያገኘውም።



ከሰለፎች

ሐሰን አልበስሪ አንድ ሰው ክፉኛ እንዳማቸው አወቁና ጣፋጭ ቴምርና አነስተኛ መልእክት ላኩለት፤ መልእክቱም ወዳጄ ሆይ እንደምን ሰንብተሀል እንዳማኸኝ ባወቅኩ ጊዜ ይህን ጣፋጭ ቴምር ላኩልህ አምተኸኛል ብዬ አምቼህ ያገኘሁትን ምንዳ በዋዛ የማስነጥቅ ሞኛሞኝ አይደለሁም የሚል ነበር።


"ንጉሶችና የንጉሶች ልጆች እኛ ያለንበትን ደስታ ቢያውቁ ኖሮ ለኛ ነው የሚገባው ብለው ይጋደሉን ነበር" -ኢብኑ ተይሚያ

አል-ዓቂዳ (العقيدة)

ለተውሂድ ቦታ ስጥ! አሏህ ከእውቀቶች ሁሉ በቅድሚያ እንድንማረው ቦታእንድንሰጠው ያዘዘን እርሱን በብቸኝነት ማምለክ ተውሂድን ነው!« ﻓَﺎﻋْﻠَﻢْ ﺃَﻧَّﻪُ ﻟَﺎ ﺇِﻟَﻪَ ﺇِﻟَّﺎ ﺍﻟﻠَّﻪُ ﻭَﺍﺳْﺘَﻐْﻔِﺮْ ﻟِﺬَﻧﺒِﻚَ ﻭَﻟِﻠْﻤُﺆْﻣِﻨِﻲﻥَ ﻭَﺍﻟْﻤُﺆْﻣِﻨَﺎﺕِ» «እነሆ ከአላህ ሌላ አምላክ አለመኖሩንም ዕወቅ፡፡ ስለ ስህተትህም ለምእመናንም ምሕረትን ለምን፡፡» (ሱረቱ አል-ሙሀመድ :19)

አል-ፊቅህ (الفقه)

★ፍቂህ ማለት መረዳት ማለት ሲሆን በዚህ  ፕሮግራማችን የምንዳስሰው ሶላትን ፣ ዘካን ፣ ፆምን ፣ ሐጅን ፣ እንዲሁም መሸጥ መለወጥን እና ዉርስን ተመሳሳይ የሆኑ ህግጋቶችን የምንዳስስበት ትምህርት ነው።
ብዙ የፊቂህ መፀሀፍቶች ሁሉም ማለት ይቻላል  ወድያውኑ የሚጀምሩት “ኪታቡ ጡሐራ” ብለው ነው።

ሲራ (السيرة)

ሙሐመድ የዐብደላህ ልጅ፣ የአብዱል ሙጦሊብ ልጅ፣ የሃሽም ልጅ፣ የመናፍ ልጅ፣ የፈህር (ቁረይሽ) ልጅ፣ የማሊክ ልጅ፣ የነድር ልጅ፣ የኪናነህ ልጅ፣ የዐድናን ልጅ፣ የአሏህ ነብይ እስማዒል ልጅ፣ የአሏህ ወዳጅ የኢብራሂም ልጅ።

አሏህ ከጥሩ ጎሳ መረጣቸው። የመሐይምነት ዘመን ቆሻሻ ወደ ዘር ግንዳቸው አልገባም።

ዓረብኛ ቋንቋ እና ሌሎችም (اللغة العربية وغيره)

ሴቶች ራሳቸውን በተለያዩ ሸሪዓዊ፣ ማህበራዊ፣ የትዳር፣ የልጅ አስተዳደግ እና የተለያዩ ውይይቶችን በማካሄድ እውቀታቸውን የሚያዳብሩበት፤ ከዚህ በዘለለም የሸሪዓ አስተምህሮትን ወደ ህይወታቸው በተጨባጭ የሚያመጡበትን ሰፋፊ የአቅጣጫ ጥቆማዎችንና የልምድ ልውውጦችን ያካሂዳሉ።

መገኛዎቻችን/Contact

ጥያቄ ወይም ሀሳብ ካለዎትከታች ባሉት አድራሻዎቻችን ሊያገኙን ይችላሉ።

አድራሻችን

ቤተል 72 ሰፈር ረያን መስጂድ

Email Us

ihsanmedresa@gmail.com

ስልክ ቁጥር

0936639603

የትምርት ሰዓት

ከሰኞ -ቅዳሜ: 10:30AM - 12:30PM;